በሃያ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ወጪ ይከናወናል የተባለው የአዲስ አበባ ወንዞች ዳርቻዎች ልማት ፕሮጀክት 30 ሺሕ ነዋሪዎችን እንደሚያስነሳ ተገለጸ፡፡ ከእንጦጦ ተራራ እስከ አቃቂ ከተማዋን ለሁለት ከፍለው በሚፈሱ ወንዞች ዙሪያ ሰፍረዋል የተባሉትን 30 ሺሕ ነዋሪዎች መልሶ ለማስፈር እንቅስቃሴ መጀመሩን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) የቴክኒክ አማካሪ ወ/ሮ መስከረም ታምሩ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ሃምሳ ስድስት ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው የወንዞች ተፋሰስ ዙሪያ ከሰፈሩት 30 ሺሕ ነዋሪዎች መካከል፣ ሕገወጥ ሰፋሪዎችም እንዳሉ ወ/ሮ መስከረም ገልጸዋል፡፡ ሕገወጥ ሰፋሪዎቹን የመለየት ሥራው በአብዛኛው የተጠናቀቀ ቢሆንም፣ በወንዞቹ ዙሪያ አሁንም ድረስ ሕገወጥ ግንባታዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ሕገወጦች በፕሮጀክቱ ለሚነሱ ነዋሪዎች በተዘጋጀው የመልሶ ማስፈር ፕሮግራም ለመካተት ሲሉ፣ አሮጌ ቆርቆሮ በውድ ዋጋ በመግዛት ነባር አሮጌ ቤት አስመስለው እንደሚሠሩ ታውቋል፡፡ ‹‹ቀደም ሲል በወሰድነው መረጃ መሠረት ነው የምንሠራው፡፡ ሕገወጦች ለማጭበርበር የሚፈጽሙት ድርጊት ዋጋ የለውም፤›› ያሉት ወ/ሮ መስከረም፣ ቀደም ሲል በተሰበሰበ መረጃ መሠረት ሕጋዊ ሆነው የተገኙት ብቻ ምትክ ቤት እንደሚያገኙ አስታውቀዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ነዋሪዎችን እያነጋገረ ሲሆን፣ በመልሶ ማስፈር ፕሮግራሙ ላይ የነዋሪዎች ፍላጎትን ለማወቅ እየተሠራ ነው ተብሏል፡፡ ለዓመታት ከኖሩበት አካባቢ ዕድርና የመሳሰሉትን ማኅበራዊ ሕይወት ጥለው ሌላ ቦታ መሄድ የሚከብዳቸው ብዙም ሳይርቅ በአካባቢው መኖሪያ እንዲያገኙ እንደሚደረግ፣ ሌላ ቦታ መስፈር የሚፈልጉም እንዲሁ በሌላ አካባቢ እንዲሰፍሩ እንደሚደረግ አማካሪዋ ገልጸዋል፡፡

በልማቱ የሚነሱ ነዋሪዎችን የማስፈሩ ፕሮግራም የከተማ አስተዳደሩ ለቤቶች በሚይዘው በጀት ውስጥ የሚካተት እንደሆነ፣ በአንድ ጊዜ ነዋሪዎች እንዳይነሱ እየታየ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ የመጀመርያው የፕሮጀክቱ ትግበራ ከእንጦጦ ተራራ እስከ ፒኮክ ወንዝ ዳርቻ የሰፈሩ ነዋሪዎችን ይነካል ብለዋል፡፡ የፕሮጀክቱ የመጀመርያ ክፍል ተግባራዊ መደረግ የሚጀምረውም በቀጣዩ ዓመት እንደሆነ አክለዋል፡፡

በ29 ቢሊዮን ብር ወጪ ተግባራዊ የሚሆነው ፕሮጀክቱ በሦስት ዓመታት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡ የከተማዋን የአረንጓዴ ሽፋን አሁን ካለበት 0.3 ወደ ሰባት በመቶ ከፍ ያደርጋልም ተብሎለታል፡፡ በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥም አራት ሺሕ ሔክታር መሬት እንደሚለማና ድልድዮች፣ ሰው ሠራሽ ሐይቆች፣ የንግድ ማዕከላትና የውኃ ትራንስፖርት ግንባታዎችን እንደሚያካትት ተነግሯል፡፡

የአዲስ አበባ ወንዞች ዳርቻዎች ልማት ፕሮጀክት አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ የማድረግ ዓላማ ሰንቋል፡፡ የወንዞች ዳርቻ የአረንጓዴ መናፈሻ የመጀመርያ ፕሮጀክት አካል የሆነው የቤተ መንግሥት አካባቢ የከተማ መናፈሻ ሥራም፣ የካቲት 14 ቀን 2011 ዓ.ም. በይፋ መጀመሩ የሚታወስ ነው፡፡ ከእንጦጦ እስከ ብሔራዊ ቤተ መንግሥት የተዘረጋው የፕሮጀክቱ የመጀመርያው ምዕራፍ 2.5 ቢሊዮን ብር እንደሚፈጅ፣ ወጪውም በከተማ አስተዳደሩ የሚሸፈን እንደሆነ ይታወቃል፡፡

9 June 2019
ሻሂዳ ሁሴን

በወንዞች ዳርቻ ልማት 30 ሺሕ ነዋሪዎች ይነሳሉ

1055total visits,2visits today

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Facebook

ፍቅርና ሰላም ለኢትዮጵያ ለዘላለሙ!!
×

Like us on Facebook