From Mayor Office of Addis Ababa

ለነዋሪዎች የመጠለያ አቅርቦት የተሻለ መሆን የአንድ ከተማ እድገት አንዱ መለኪያ ነው ፡፡ በፈጣን እድገት ላይ የምትገኘው መዲናችን አዲስ አበባም ቤትን ጨምሮ ከፈጣን እድገቷ ጋር ተያይዞ ያለው ሰፊ የአገልግሎት አቅርቦት ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ይገኛል ፡፡ ከእነዚህ መካካልም አንዱና ዋነኛው የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ነው ።

የከተማ አስተዳደሩ የመኖሪያ ቤት ዕጥረትን ለማቃለል ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ከፍተኛ በጀት በመመደብ ሰፋፊ የቤት ልማት ሥራዎችን ሲሰራ ቆይቷል ፡፡

በዚህ እንቅስቃሴ በባለፉት ዓመታት ከ178,000 ቤቶች በላይ ተገንብተው በ12 የተለያዩ ዙሮች ለተመዝጋቢዎች በዕጣ ተላልፈዋል ።

 

አሁን ያለው የለውጥ አመራርም ሰፊ የመጓተትና የህዝብ ጥያቄ ሲነሳባቸው የነበሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ግንባታ የተለየ ትኩረት በመስጠት ለማጠናቀቅ የቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ፡፡

በዚህም መሰረት በግንባታ ሂደት ላይ ከሚገኙ 132 ሺህ ቤቶች መካከል፤ በዚህኛው ዙር በሁለቱም የቤት ልማት ፕሮግራም ማለትም በ20/80 እና በ40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም ተገንብተው ግንባታቸው በመገባደድ ላይ የሚገኙ ቤቶች በዕጣ ለተመዝጋቢዎች ለማስተላለፍ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ነው ።

በዕጣ ለመተላለፍ ዝግጁ የሆኑ 32,653 የ20/80 እና 18,576 የ40/60 በድምሩ 51,229 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ናቸው። ከዚህ በፊት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣን ለማውጣት የከተማ አስተዳደሩ ሲጠቀምበት የነበረውን የዕጣ ማውጫ ሲስተም የነበሩበትን ቴክኒካል ክፍተቶችን በመለየት፤ የሁለቱንም የቤት ልማት ፕሮግራም (የ20/80 እና የ40/60) ዕጣ ማውጫ ሲስተም እንደ አዲስ በማበልፀግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመገናኛና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ በዕጣ ማውጫ ሲስተም ላይ የሙከራ ሥራን በመስራት ሲስተሙ በትክክል እንደሚሰራ ማረጋገጫ ተሰጥቷል። በ20/80 የቤት ልማት ፕሮግራም በዕጣ ከሚተላለፉ 32,653 ቤቶች መካከል ስቱዲዮ 1,248፣ ባለ 1 መኝታ 18,823፣ ባለ 2 መኝታ 7,127፣ ባለ 3 መኝታ 5,455 ቤቶች ናቸው። በዚህኛው ዙር በ20/80 የቤት ልማት ፕሮግራም በስቱዲዩ፣ በባለ 1 እና በባለ 2 መኝታ ቤቶች ዕጣ ተጠቃሚ የሚሆኑት የ97 ዓ/ም ተመዝጋቢዎች ሆነው ምዝገባቸውን በ2005 ዓ/ም ነባር ተመዝጋቢ ብለው ያደሱ ሲሆኑ በባለ 3 መኝታ ቤቶች ዕጣ ተጠቃሚ የሚሆኑት የ2005 ዓ/ም አዲስ ተመዝጋቢዎች ናቸው፡፡

 

ለነባር ተመዝጋቢዎች ዕጣ ውስጥ ለመግባት ዝቅተኛ የቁጠባ መጠን ቢያንስ ለተከታታይ 40 ወራት የቆጠቡ ነባር ተመዝጋቢዎች ሲሆን ለአዲስ ባለ 3 መኝታ ተመዝጋቢዎች ዕጣ ውስጥ ለመግባት ዝቅተኛ የቁጠባ መጠን ቢያንስ ለተከታታይ 60 ወራት የቆጠቡ አዲስ ተመዝጋቢዎች ይሆናሉ። በ20/80 በዕጣ ከሚተላለፉ ቤቶች መካከል 5% ለአካል ጉዳተኞች፣ 20% ለመንግስት ሠራተኞች፣ 30% ደግሞ ለሴቶች በኮታ ዕጣ ውስጥ የሚካተቱ ይሆናሉ።

 

በዚህም መሠረት ለ13ኛው ዙር የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ውስጥ ለመግባት የሚያስፈልገው ዝቅተኛው የቁጠባ መጠን ለስቱዲዮ 6,040 ብር፣ ለባለ 1 መኝታ 10,960 ብር፣ ለባለ 2 መኝታ 22,560 ብር እና ለባለ 3 መኝታ 29,340 ብር ይሆናል። በ13ኛው ዙር የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከሚተላለፉ ቤቶች መካካል የስቱዲዮ ስፋት ከ28 እስከ 32 ካሬ ሜትር፣ የባለ 1 መኝታ ስፋት ከ44 እስከ 66 ካሬ ሜትር፣ የባለ 2 መኝታ ስፋት ከ69 እስከ 81 ካሬ ሜትር ሲሆን የባለ 3 መኝታ ካሬ ሜትር ከ92 እስከ 129 ካሬ ሜትር ነው። በ2ኛው ዙር የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች በዕጣ ከሚተላለፉ 18,576 ቤቶች መካከል ባለ 1 መኝታ 3,060፣ ባለ 2 መኝታ 10,322፣ ባለ 3 መኝታ 5,194 ቤቶች ናቸው።

ለ2ኛው ዙር የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ውስጥ ለመግባት የሚያስፈልገው ዝቅተኛው የቁጠባ መጠን ለሁሉም የመኝታ ዓይነት በምዝገባው ወቅት ከነበረው ጠቅላላ ዋጋ ውስጥ 40% እና ከዚያ በላይ የቆጠቡ በዕጣው ተወዳዳሪ ይሆናሉ። በዚህም መሠረት ለ2ኛው ዙር የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ውስጥ ለመግባት የሚያስፈልገው ዝቅተኛው የቁጠባ መጠን ለባለ 1 መኝታ 65,058 ብር፣ ለባለ 2 መኝታ 100,000 ብር እና ለባለ 3 መኝታ 154,560 ብር ይሆናል።

በ40/60 በዕጣ ከሚተላለፉ ቤቶች መካካል 20% ለመንግስት ሠራተኞች በኮታ ዕጣ ውስጥ የሚካተቱ ይሆናሉ። በ2ኛው ዙር የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከሚተላለፉ ቤቶች መካካል የባለ 1 መኝታ ስፋት ከ57 እስከ 61 ካሬ ሜትር፣ የባለ 2 መኝታ ስፋት ከ68 እስከ 122 ካሬ ሜትር ሲሆን የባለ 3 መኝታ ስፋት ከ76 እስከ 123 ካሬ ሜትር ነው።

በ20/80 የቤት ልማት ፕሮግራም ተገንብተው በዕጣ ለመተላለፍ ዝግጁ ለሆኑ ቤቶች መንግስት የመሠረተ ልማት እና የመሬት የሊዝ ዋጋን ሙሉ በሙሉ ድጎማ በማድረግ የ13ኛው ዙር የማስተላለፊያ የካሬ ዋጋ 4,511.27 ብር ይሆናል፡፡ ይህም ማለት መንግስት በዚህኛው ዙር ለሚተላለፉ የ20/80 ቤቶች፤ የመንገድ መሠረተ ልማት ወጭን ሳይጨምር ለአንድ ቤት በአማካይ 64,502.41 ብር ድጎማ አድርገዋል።

በ40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም ተገንብተው በዕጣ ለመተላለፍ ዝግጁ የሆኑ የቤቶች ጠቅላላ የግንባታ፣ የመሠረተ ልማት እና የመሬት ሊዝ ወጭ አማካይ የካሬ ሜትር ዋጋ 8,404.42 ብር ሲሆን መንግስት የመንገድ መሠረተ ልማት እና የመሬት የሊዝ ዋጋን ሙሉ በሙሉ ድጎማ በማድረግ የ2ኛው ዙር የማስተላለፊያ የካሬ ዋጋ 6922.14 ብር ይሆናል፡፡

ይህም ማለት መንግስት በዚህኛው ዙር ለሚተላለፉ የ40/60 ቤቶች ለአንድ ካሬ ሜትር 1,482.28 ብር ድጎማ አድርገዋል። በሁለቱም የቤት ልማት ፕሮግራም የሚተላለፉ የቤቶች የህንጻ ግንባታ ሥራ በአማካይ ከ80 በመቶ በላይ ግንባታቸው የተጠናቀቁ ናቸው፡፡ ቤቶቹ በሚተላለፉባቸው የግንባታ ሳይቶች የመንገድ፣ የፍሳሽ፣ የውሀና የመብራት መሰረተ ልማቶች በተቀናጀ ዕቅድ እየተሰሩ የሚገኙ ሲሆን ግንባታቸው በዓመቱ መጨረሻ የሚጠናቀቁ ሲኖሩ፤ በ2012 ዓ.ም አጋማሽ ላይም የሚጠናቀቁም ይኖራሉ፡፡

 

ቀሪው የቤቶች የህንጻ የግንባታ እና የመሰረተ ልማት ሥራዎች ዕጣ የወጣላቸው የቤት ባለቤቶችን በተለያዩ መንገዶች በሚያሳትፍ ሂደት ተሰርተው እንዲጠናቀቁ ይደረጋል። ላለፉት በርካታ ዓመታት፤ ምንም እንኳን መንግስት የአዲስ አበባ ከተማን የመኖሪያ ቤት ዕጥረት ለመቅረፍ ከፍተኛ በጀት እና በርካታ የሰው ሀይልን መድቦ ሲሰራ የነበረ ቢሆንም ከተመዝጋቢዎች ቁጥር እና ከከተማው የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ጋር ሲነፃፃር የተመዘገበው ውጤት በጣም ዝቅተኛ ነው።

የከተማ አስተዳደሩ በባለፉት 14 ዓመታት በቤት ልማት ፕሮግራም ላይ የነበሩ ክፍተቶችን እና ማነቆዎችን በመለየት በሀገር ደረጃ በተቀመጠው ፖሊሲ እና ስትራቴጂ መሠረት ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ምርጥ ተሞክሮዎችን በመውሰድ የቤት ልማቱን ፕሮግራም በተለየ መልኩ እና በልዩ ትኩረት ለመምራት ዕቅድ ይዘው ወደ ተግባር ለመግባት በዝግጂት ላይ ይገኛል። ከእነዚም መካካል የጋራ መኖሪያ ቤት ልማት ላይ የተመለመሉ ተቋራጮች ራሳቸው የሚያስፈልገውን የግንባታ ግብዓት አቅርበው (Supply and Fix method) መንግስት ደግሞ ስታንዳርድ፣ ጥራት፤ በጀት እና ጊዜን እየተቆጣጠረ የሚሄድበትን ሥርዓት መዘርጋት፣ ማህበራትን በማደራጀት መንግስት መሬትን በማቅረብ በቅርበት ድጋፍ እና ክትትል እያደረገ የመኖሪያ ቤት የሚያለሙበትን ሥርዓት መዘርጋት፣ የመንግስትና የግል ዘርፍ አጋርነትን (Public Private Partnership) በመፍጠር የመኖሪያ ቤት የሚያለሙበትን ሥርዓት መዘርጋት፤ ከውጭ እና ከሀገር ውስጥ የቤት አልሚ ድርጅቶች ጋር ሽርክናን በመፍጠር (Joint Venture) የመኖሪያ ቤት የሚያለሙበትን ሥርዓት መዘርጋት፤ መንግስት እና በጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በመሆን የመኖሪያ ቤት የሚያለሙበትን ሥርዓት መዘርጋት ይገኙበታል።

ከላይ የተገለፁትን የቤት ልማት አማራጮችን በመጠቀም፤ ከዚህ በፊት የነበረውን የቤት ፈለጊ እና የአቅርቦት ሰፊ ልዩነትን ለመቅረፍ እና ለማጥበብ በትጋት ይሰራል።

51 ሺህ 229 የጋራ መኖሪያ ቤቶች የፊታችን ረቡዕ ለተጠቃሚዎች ይተላለፋሉ!!

1983total visits,1visits today

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Facebook

ፍቅርና ሰላም ለኢትዮጵያ ለዘላለሙ!!
×

Like us on Facebook